የሀገር ውስጥ ዜና

አገልግሎቱ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ሕንፃ አስመረቀ

By Tamrat Bishaw

February 24, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃሕፍት አገልግሎት ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ባለ 17 ወለሎች ሕንፃ አስመረቀ።

በመንግስት ወጪ የተገነባው ይህ ሕንፃ የመዛግብት ማከማቻ እንደመሆኑ ዘመኑን ባገናዘበ መልኩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ህንፃው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ አንባቢያን፣ መፅሐፍ አዟሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው የተመረቀው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመትም ከህንፃው ምረቃ ጋር በድምቀት አክብሯል።

በስነ-ስርዓቱ ወቅት ባለፉት 80 ዓመታት በተለያዩ መልኩ የተከተቡ መፅሐፍት፣ ቅርሶች እና የድምፅ ታሪኮች እንዲሁም ለቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሐፍት የተሰጡ የመጽሐፍት ስጦታዎች ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቱሩፋቶችን የሚያሳይ ታሪክን ከትበው፣ ሁነትን መዝግበው፣ ጥበብንና እውቀትን አስፍረው የጽሁፍና የቃል ታሪካዊ ቅርሶች በበቤተ መዛግብትና ቤተ መፅሐፍት መኖራቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ማንነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ታሪክ ይሰራል ታሪክም ይደገማል፤ ታሪክ ሲሰራና ሲደገም ግን ከፍ ብሎ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአነስተኛ ቤት ስራ የጀመረው የተቋሙ ስራ ዛሬ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረፉን አንስተዋል።

በስነስርዓቱ ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ደራሲያንና አንባቢያን ተገኝተዋል።

ቅድስት ተስፋዬ