አሰባሳቢ የወል ትርክቶችን የመገንባትና ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው – አቶ ተስፋዬ በልጅጌ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሰባሳቢ የወል ትርክቶችን የመገንባትና ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።
በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ እንዳሉት ፥ የኢትዮጵያን እምቅ ሃብትና የመልማት አቅም እውን ለማድረግ መንግስት አቅሙን አስተባብሮና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታትም ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ የልማት ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ክብርና አንድነት ማስጠበቅ መቻሉንም ገልጸዋል።
የውስጥና የውጭ የጥፋት ሃይሎች ኢትዮጵያን የመበታተን እቅድ በመያዝ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አስታውሰው ፥ እነዚህን እኩይ ዓላማዎች በማክሸፍ ሀገርን ማስቀጠል መቻሉንም ነው ያነሱት።
ከዲፕሎማሲ አንጻር የተጀመሩ ስራዎችም አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ጠቅሰው ፥ የባህር በር ለማግኘት የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችም በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከውድቀት የታደገ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ መከናወኑን የጠቀሱት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ፥ ቀደም ሲል የቆሙ ፕሮጀክቶችንም ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያንን ብዝሃነትና አንድነት የሚያደበዝዙ የተዛቡ ትርክቶች መኖራቸውን አስታውሰው ፥ እነዚን የማረምና የማስተካከል ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም የተሳሳቱና ከፋፋይ ትርክቶችን በማረም የወል ትርክት በመገንባትና ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ስራ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠየቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አሰባሳቢ ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ፥ በንግግርና የሃሳብ የበላይነት የሚራመድ የፖለቲካ ባህልና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በአዲስ አበባ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ፥ በሂደት የማሟላትና ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አወል አርባን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።