ሃገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው ሃገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን በዛሬው እለት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።
የአረንጓዴ አሻራው ቀን በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር እቅዳችን እናሳካለን፤ ሃገራችን አረንጓዴ እናደርጋለን ብለዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የተጀመረ ሲሆን፥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሐሰንም በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ተሳትፈዋል።
በአማራ ክልል በተያዘው ክረምት 1 ነጥብ 75 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መግለጹ ይታወሳል።
በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደግሞ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ነው የሚጀመረው፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሀዋሳ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ፥ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በተገኙበት ነው የተካሄደው።
ሁሉም ህብረተሰብ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም መርሃ ግብር ግብ እንዲሳካ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በዚህ ወቅትም በክልሉ 40 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይም በሐረሪ ክልልም መርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በክልሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።
በሶማሌ ክልልም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፥ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁሉም አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ በዘንድሮው ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል መታቀዱም ተጠቅሷል።
ህብረተሰቡም ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመጠበቅ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር በመተግበር በችግኝ ተከላ ዘመቻው ላይ እንዲሳተፍም መልዕክት አስተላልፈዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።