የህዝቡን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በተሰራ ሥራ ውጤት ተገኝቷል – ሌ/ል ጄ/ል መሠለ መሰረት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝቡን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በተሰራ ሥራ ውጤት ተገኝቷል ሲሉ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሰረት ገለጹ፡፡
ሌተናል ጄኔራል መሰለ መሠረት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በመገኘት ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በወቅታዊ ፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም በአካባቢው የሚገኘውን የሸኔ ፀረ-ሰላም ሃይል ለማጥፋት የአመራሩ ቅንጅትና ትብብር አሥፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሸባሪው የሸኔ ቡድን በመንግስት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የሽፍትነት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉ ያነሱት ጄኔራል መኮንኑ፥ ሠራዊቱ የህዝቡን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ሌሊትና ቀን ያለ እረፍት በመስራት ውጤቶች መገኘታቸውንም ነው የገለጹት።
የዕዙ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ብርጋዲየር ጄኔራል አማረ ባህታ በበኩላቸው፥ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ ሲቪልና ፀጥታ አመራሩ በሁሉም መስክ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ አሁን የተጀመረውን ውጤታማ ስራ ለማስቀጠል በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መርሳ ፊጣ፥ የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም ሠራዊቱ ባልሰፈረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በህብረተሰቡ አስነዋሪ ድርጊት እየፈፀመ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም አሁን ላይ ሠራዊቱ ወደ ቀጠናው ዘልቆ በመግባት ለህዝቡ ሰላም ከማስፈን በተጨማሪ የመሰረተ ልማት አውታሮችም አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መሠራቱንም ነው የገለጹት።
በዚህም ህዝቡ ለሠራዊቱ ያለውን ክብርና ፍቅር በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለፁ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡