Fana: At a Speed of Life!

በመኖሪያ ቤት የጦር መሳሪያና ገንዘብ ሸሽገው የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመኖሪያ ቤት ውስጥ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ሸሽገው የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ጠመንጃ፣ ሽጉጥ፣ ጥይት እና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በኤግዚቢትነት ተይዟልም ተብሏል፡፡

በጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የቀጨኔ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በጦር መሳሪያ ዝውውር በሚጠረጠር ግለሰሰብ ላይ ክትትል በማድረግና ማስረጃ በማሰባሰብባ በክፍለ ከተማው ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨፊ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት በሕግ አግባብ ባደረገው ብርበራ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያና በሕገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ገንዘብ መያዙን ገልጿል፡፡

በግለሰቡ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ አንድ ኤስኬኤስ ጠመንጃ ከመሰል 30 ጥይት ጋር፣ አንድ ክላሽንኮቭ ከ72 ጥይት እና አንድ ኮልት ሽጉጥ ከ8 ጥይት ጋር እንዲሁም 1 ሚሊየን 294 ሺህ 700 ብር እንደተገኘ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሩፋኤል አካባቢ ፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ አድርጎ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል ባካሄደው ብርበራ አንድ ክላሽንኮቭ ከ90 ጥይት እና ሁለት ኮልት ሽጉጥ ከ29 ጥይት ጋር በኤግዚቢትነት መያዙንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ወንጀለኞች ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያን በመጠቀም ሊፈፅሙ የሚያስቡትን ወንጀል አስቀድሞ ለማክሸፍ መረጃን መነሻ በማድረግ የሚያከናውነውን የቁጥጥር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መገለጹን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.