የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን መረጣ ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወላይታ ዞን በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህብረሰብ ተወካዮችን መረጣ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ 12 ዞኖች ከዚህ በፊት ባሰለጣናቸው ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተወጣጡ ተባባሪ አካላት ታግዞ ነው አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች ልየታን እያካሄደ የሚገኘው፡፡
በዚህም ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም በወላይታ ዞን ከ23 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ የተወካዮች መረጣ እንደሚከናወን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተወካዮች መረጣ ላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
መረጣው አካታች፣ ግልጽ፣ አሳታፊና እና ተዓማኒ እንዲሆንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በሂደቱም ከእያንዳንዱ የማሕበረሰብ ክፍል ሁለት ተወካዮች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር እንደሚመረጥ ጠቁመዋል፡፡
በማስተዋል አሰፋ