Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያና ሩሲያ ወዳጅነት በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልጽግና ፓርቲ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል የፓርቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪን በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት በመገኘት ከብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ሀላፊ ተስፋሁን ጎበዛይ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ÷ ኢትዮጵያና ሩሲያ በተለያዩ መስኮች ጠንካራ ግንኙት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ሩሲያ በተለያዩ ጊዜ ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታዎች በገጠሟት ቁጥር ከጎኗ መቆሟን በመግለጽ፤ ለዚህም ብልፅግና ፓርቲ ያለው ክብር ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሁለትዮሽ ውይይቱ ላይ በቀጣይ የሁለቱ መንግስታት እና ፓርቲዎችን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ዙሪያም መክረዋል፡፡

የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለመስጠትና ተባብሮ ለመስራት የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነትን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

በቅርቡ በዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ አዘጋጅነት የተከናወነው የዘመናዊውን ቅኝ ግዛት ስርአትን የሚቃወሙ ሀገራት ፎረም ምስረታ ላይ ብልፅግና ፓርቲ ላደረገው ተሳትፎ ዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ምስጋናው የላቀ እንደሆነ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኺን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ስትዋጋ ያሳለፈች መሆኗ በውይይቱ የተገለጸ ሲሆን÷ አሁንም በፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ሊገለጥ የሚችለውን አዲሱን የቅኝ አገዛዝ መንገድ ለመከላከል የገለልተኝነት መርህን በጠበቀ መልኩ እንደምትሰራ ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይም የፓርቲም ሆነ መንግስታዊ ግንኙነቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጅምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግባባት ላይ መደረሱን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.