የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በተለዩ የሥራ መስኮች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለዩ የሥራ መስኮች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ዋና ዳይሬክተር ጆናታን ንዛይኮሬራ ጋር በግብርና ዘርፍ አብሮ መሥራት በሚችሉበት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በዝናብ ጥገኝነት የሚፈለገውን የግብርና ዘርፍ እድገት ማምጣት እንደማይቻል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጀመረችው ስንዴንና ሩዝን በመስኖ የማልማት ሥራ የባንኩ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የግብርና እድገትን የሚያፋጥኑ መሰረተ-ልማቶችን ለማሟላት፣ በአርብቶ አደሮች አካባቢ የውኃ እጥረትን ለመፍታት፣ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምን ለማሳካት፣ ዘመናዊ እንስሳት መኖ ልማትን ለማስፋት እና ለአቅም ግንባታ ሥራዎች ባንኩ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ጆናታን ንዛይኮሬራ በበኩላቸው÷ ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ 22 ፕሮጀክቶች እንዳለው መናገራቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በተለዩት የሥራ መስኮችም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ባንኩ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡