የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግብፅ የውሃ ፍላጎት ጋር ግጭት እንደሌለው ቻይና ትገነዘባለች – አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግብፅ የውሃ ፍላጎት ጋር ግጭት እንደሌለው ቻይና እንደምትገነዘብ በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ቻይና የራሷን የመልማት መብት እንደምታስከብር ሁሉ የኢትዮጵያን የመልማት መብት ተገንዝባ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልፀዋል።
በተፈጥሮ ሀብታቸው የመልማት እንቅስቃሴያቸውን አንድም ጊዜ ለድርድር አቅርበው ለማያውቁት ቻይናዎች ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ግድብ በታችኞቹ ተፋሰስ አባል ሀገራት ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማያሳድር እና የራሳችንን ህልውና ለማስቀጠል የጀመርነው ፕሮጀክት መሆኑን እያስረዳን ነውም ብለዋል።
ቤጂንግም ሶስቱ ሀገራት ልዩነታቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሰላማዊ ድርድር እንዲፈቱ በየጊዜው አቋሟን እየገለፀች መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የዲፕሎማሲ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎንም ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ርብርብ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራም በኤምባሲው በኩል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ሆኖ በአራቱም ማዕዘን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ርብርብ እያደረጉበት ያለ ብሔራዊ ፕሮጀክት መሆኑን አውስተዋል።
ቻይና እንደ ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ቱርክ፣ ህንድ እና አሜሪካ የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገር ስትሆን ከአሁን በፊት ከግዛቷ የሚፈልቁ ወንዞች እና ጅረቶችን ለልማቷ ተጠቅማለች ነው የተባለው።
በርካታ ግድቦችንም ገንብታ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ለቁጥር የሚያዳግቱ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎቿን የሃይል ፍላጎት ያሟላች መሆኗም ተነስቷል።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋም በሌሎች ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ የማይገባ ገለልተኛና ለአብሮ መልማት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑም ይነገራል።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያም የያዘችው አቋምም ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በሰጣት ሀብት የመልማት መብት አላት የሚል ነው።
ከድህነት መውጣት እንዳለባት የሃይል አቅርቦት እጥረቷን መቅረፍ እንደሚገባት ታምናለችም ብለዋል አምባሳደር ተሾመ ቶጋ።
በስላባት ማናዬ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።