እንግሊዝና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የተመራ ልዑክ ከዓረብ ኤሚሬቶች እና ከእንግሊዝ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
ውይይቱ በአቡዳቢ እየተካሄደ በሚገኘው 13ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ጎን ለጎን ነው የተደረገው፡፡
በዚህ መሰረትም ልዑካኑ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የንግድ ሚኒስትር ዴዔታ ታኒ ቢን አህመድ አል ዘዩዲ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት መስፈርቶችን ለማጠናቀቅ እያደረገች ያለውን ጥረት እና ሒደቱ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል::
በተመሳሳይ የኢትዮጵያልዑክ ከእንግሊዝ የንግድ ፖሊሲ ሚኒስትር ዴዔታ፣ የፓርላማ አባል እና የለንደን ሚኒስትር ግሬግ ዊሊያምስ ሃድስ ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም የእንግሊዝ ልዑካን ቡድን አባላት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ለማጠናቀቅ ለጀመረችው ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
እንግሊዝ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችውን ጥረት እና የእስካሁኑን ጉዞ ማድነቃቸውም ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት ጉልህ የገበያ ስፋትና ኢኮኖሚ አንፃር የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ ለራሷም ሆነ ለሌሎች አባል ሀገራት ሁለንተናዊ ጥቅም እንዳለውም አፅንኦት ሰጥተዋል።