Fana: At a Speed of Life!

128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የሰራዊታችንን ድሎችና አኩሪ ገጽታ በሚያጎላ መልኩ ይከበራል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የሰራዊታችንን ድሎችና አኩሪ ገጽታ በሚያጎላ መልኩ ይከበራል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አከባበርን በተመለከተ እንደተናገሩት ፥ አምና 127ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አከባበርን የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲያስተባብር ተደርጎ ከፍተኛ በሆነ ሀገራዊ ንቅናቄ በድምቀት መከበሩ ይታወሳል።

ዘንድሮም 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ካለፈው የተገኙ በርካታ ልምዶች ተወስደው በተለየ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች ሲካሄዱ እንደነበርም ነው የገለጹት።

ቅድመ ዝግጅቱን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፥ ከጀግኖች አባቶቹ ጽኑ እሴትን የወረሰውን የአሁኑ ሰራዊታችንን መልካም ድሎችና አኩሪ ገጽታ በሚያጎላ መልኩ የሚከበር ይሆናል ብለዋል።

የዘንድሮ 128ኛ የዓድዋ ድል በዓል ፥ ድሉን ለመዘከር በተገነባው ግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ እንደሚከበርም አስታውቀዋል፡፡

በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ፣ በከተማ አስተዳደሮች በተቋማት፣ በመላው ዓለም በሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ይከበራል ብለዋል፡፡

ቅዳሜ በሚከበረው 128ኛው የአድዋ ድል በዓል የተለያዩ ታሪካዊ ወታደራዊ ትዕይንቶች፣ ጥበባዊ ክዋኔዎች እና ሌሎችም መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.