Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሺህ ግራም በላይ ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ ይዞ ተገኝቷል በተባለ ግለሰብ ላይ ክስተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ 3 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው 1 ሺህ 10 ነጥብ 95 ግራም ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ ይዞ ተገኝቷል በተባለ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ አማረ ዮሐንስ ተ/ጊዮርጊስ ላይ ሁለት ክሶችን መስርቷል።

አንደኛው ክስ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 21 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሹ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:40 ላይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ በረራ አካባቢ ተደረገ ፍተሻ በለበሰው ጃኬት ውስጥ 3 ሚሊየን 189 ሺህ 506 ብር ከ32 ሳንቲም የሚገመት 1 ሺህ 10 ነጥብ 95 ግራም የሚመዝን ጥፍጥፍ ወርቅ ይዞ ተገኝቷል የሚል ነው፡፡

በተያዘበት ጊዜም ፈቃድ እንደሌለውና ነጋዴ እንዳልሆነ ገልጾ በወቅቱ ለነበረው ፖሊስ አዛዥ ከያዘው ወርቅ ላይ ግማሹን “ልስጥህና ልቀቀኝ” በማለት ጉቦ ያቀረበ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ÷ ተገቢ ያልሆነ ጉቦ ወይም ጥቅም መስጠት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

እንዲሁም ሁለተኛው ክስ የማዕድን አዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 7 ንዑስ ቁጥር 2 ስር እና አንቀጽ 78 ንዑስ 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የፀና ፈቃድ ሳይኖረው የተፈጥሮ ማዕድን መያዝ የሚል ነው፡፡

ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰው ከተደረገ በኋላ ከጠበቃ ጋር ተማክሮ እንዲቀርብ በይደር ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.