በሲዳማ ክልል የኩላሊት እጥበት ሊያከናውን የሚችል ሆስፒታል መሰራቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤናው ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት የኩላሊት እጥበት ሊያከናውን የሚችል ሆስፒታል በይርጋለም መሰራቱን የሲዳማ ክልል ገለጸ፡፡
የክልሉ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር አፈፃፀም በምክር ቤት መገምገሙን ተከትሎ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ወሰኔለህ ስምኦን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ ማህበራዊ፣ መሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ላይ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
“በትምህርት ዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ትምህርት ቤቶችን የማደስና የመምህራንንም አቅም የማሳደግ ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በባለሀብቶች እገዛ ትምህርት ቤቶች መገንባቸውን ጠቅሰዋል።
በጤና ዘርፍም ተመሳሳይ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ገልጸው÷ “የኩላሊት እጥበት ሊያከናውን የሚችል ሆስፒታል በይርጋለም ተሰርቷል” ብለዋል።
የይርጋለም ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደገባ በመግለጽ ከኩላሊት እጥበት በተጨማሪ ሆስፒታሉ ኦክሲጅን ማምረት እንዲችል ተደርጎ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ወሰንየለህ÷ በመንገድ ልማት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ መከወናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለመገንባት በክልሉ የፈጠራ ስራን ለማበረታታት ወጣቶች ክህሎታቸውን የሚያሳዩበትን መንገድ እንዲመቻችላቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጥላሁን ይልማ እና ታመነ አረጋ