የዓድዋ ድል የተገኘው በኢትዮጵያውያን ፍቅር፣ ሕብርና ትብብር ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድልን ማሳካት የተቻለው በህብር፣ ፍቅርና ትብብር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ዓድዋ ዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር በዓድዋ የድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት በተባበረ ክንዳቸውና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸው ወራሪ ኃይልን በማንበርከክ የሀገራቸውን ክብር አፅንተዋል።
የዓድዋ ድል በህብር፣ በፍቅርና በትብብር የተገኘ ግዙፍ ድል መሆኑን ጠቅሰው÷ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጦርም በህብረ ብሔራዊ አንድነት የተዋቀረ ሃይል መሆኑንም አንስተዋል።
የዓድዋ ዘማቾች ህብርነት የብሔር ብቻ ሳይሆን የመሪና የህዝብ፣ የከያንያንና የስንቅ አዘጋጆች፣ የሴቶች እንዲሁም ሁሉም ህብረት በመፍጠር ለሀገር ክብር የተመሙበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ዛሬም የኢትዮጵያን ጠላቶች ለማንበርከክ፣ ድህነትን ድል ለማድረግና ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማሸነፍ ህብር ሆኖ መዝመት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓድዋ ዘመን የታየው የሀገርና የወገን ፍቅር ዛሬም ፀንቶ እንዲቀጥል መሥራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ከምንም በላይ ነው ብለዋል፡፡
ዓድዋ ሀገር የሚታደግና የሚያጸና ትምህርት ቤት በመሆኑ ስብራቶችን ለመጠገን ፍቱን መድሃኒት እንደሆነም አመላክተዋል።
በመሆኑም ከቀደምት ጀግኖች የሀገር ፍቅርን በመውረስ ለሀገር ሰላምና ብልፅግና እንዲሁም ለሀገረ መንግስት ግንባታ መትጋት የዚህ ዘመን ትውልድ ሃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።