የዓድዋ ድል ለጋራ ማንነት ግንባታ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነት ግንባታ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ የዓድዋ ድል በታሪክ ዓለም የሚያውቀው እና ለሁሉም አፍሪካውያን የነጻነት አርማ ሆኖ እንደሚዘከር አውስተዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ማንነታቸውን የሚናገሩበት እና ጥቁሮች ነጮችን ድል የተቀዳጁበት ሁነት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የምንጊዜም ታሪክ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ በኩራት የሚተላለፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያን ስናከበር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲሁም ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በማጉላት መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡