Fana: At a Speed of Life!

በዓድዋ ያገኘነውን አሸናፊነት አስቀጥለን ድህነትን በማሸነፍ ትውልዳችንን ወደ ብልፅግና ከፍ እናደርጋለን – አቶ ደስታ ሌዳሞ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓድዋ ያገኘነውን አሸናፊነት አስቀጥለን ድህነትን በማሸነፍ ትውልዳችንን ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ እናደርጋለን ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም፤ የዓድዋ ድል የነጮች የበላይነትንና የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን የሚያቀነቅኑትን ያሳፈረና ያስደነገጠ ነው ብለዋል።

ድሉ የኢትዮጵያን ልዕልና ያስጠበቀ፣ የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ አንድነትና ጀግንነት የተንፀባረቀበት፣ የአፍሪካዊያንን የአሸናፊነት ስነ ልቦና ከፍ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

አውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ሊሳካ ያልቻለው አባቶቻችን በአንድነትና በህብረት፣ በቆራጥነትና በጀግንነት ባደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል።

ድሉ ጥቁር ህዝቦች ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን እንዲሰንቁና ብሎም ለነፃነታቸው እንዲታገሉና አሽናፊነትን እንዲጎናፀፉ ያስቻለ እንደሆነ አንስተዋል።

ዛሬም ይህ ትውልድ ዘመናዊ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማሸነፍ የሚችለው ድህነትንና ኋላቀርነትን አሸንፎ ሀገራችንን የብልፅግና ከፍታ ላይ ሲያሻግር ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

የዓድዋ ድል ሲታሰብ ህብረብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ህብረትን፣ ቆራጥነትን፣ የአላማ ፅናትን፣ ጠንካራ ስነልቦናን፣ ጀግንነትን፣ ድልና ድምቀትን፣ ነፃነትን፣ የያዙ ታሪካዊ አውዶች በኢትዮጵያዊያን ውስጥ እንደሚታወሱ ገልጸዋል።

ድሉ የኢትዮጵያዊነታችንን ሃያልነት በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ህያው ሆኖ እንዲኖር ያደርጋል በማለት ገልጸው፤ በዓድዋ ያገኘነውን አሸናፊነት አስቀጥለን ድህነትን በስራና በቆራጥነት አሸንፈን ትውልዳችንን ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ እናደርጋለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.