ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ በርካታ የተሽከርካሪ ጎማ፣ ቸርኬና ከመንዳሪ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
አንድ ግለሰብ በአዲስ አበባ ጦር ኃይሎች አካባቢ አራት የመኖሪያ ክፍሎችን በመከራየት በኮንትሮባንድ ያስገባቸውን የተሽከርካሪ ጎማዎችና ብዛት ያላቸው ቸርኬዎች እንዲሁም ከመንዳሪዎችን ማከማቸቱ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
በተደረገ ብርበራም ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው 695 የመኪና ጎማ ፣ 58 ቸርኬና 32 ከመንዳሪን ከእነ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የተያዙትን ንብረቶች ለአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ማስረከቡን የገለፀው ፖሊስ በግለሰቡ ላይ አስፈላጊውን ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።