Fana: At a Speed of Life!

በደብረብርሀን ከተማ በ323 ሚሊየን ብር ወጪ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረብርሀን ከተማ በ323 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚገነባዉ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ።

የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በወቅቱ እንዳሉት÷ ግንባታው በከተማው ያለውን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር የሚፈታ ፕሮጀክት ነው።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በከተሞች የሚታየውን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለመፍታት በባህር ዳር፣ ደሴና ጎንደርና ተመሳሳይ ፕሮጀክት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በደብረ ብርሀን ከተማ የሚገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ በ323 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግበትም ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)÷ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ አሁን የተጀመረው ፕሮጀክት ችግሩን እንደሚፈታ አመልክተው፤ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የፌዴራል መንግስትና የዓለም ባንክ ለፕሮጀክቱ ላደረጉት የገንዘብ ድጋፍም አመስግነዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 131 ሜትሪክ ኩብ የፍሳሽ ቆሻሻ የሚያጠራቅምና የሚያጣራ ሲሆን ተጣርቶ የሚመነጨዉ ዉሃ  ለመስኖ ልማትና ለኮንስትራክሽን አገልግሎት ይውላል ተብሏል፡፡

በግርማ ነሲቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.