Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፍ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር መከላከያ ክትባት ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ ሚኒስቴሩ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ለሚሆኑ 14 አመት ለሆናቸው ሴት ልጆች ክትባቱ መሰጠቱን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ክትባቱ በሁለት ዙሮች ይሰጥ የነበረ ሲሆን÷ በአለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ምርምር አንድ ጊዜ ብቻ መሰጠቱ በቂ መሆኑ በመረጋገጡ ክትባቱ ከዚህ ዓመት ጀምሮ አንድ ጊዜ ብቻ ይሰጣል ነው የተባለው።

በዛሬው ዕለት የተጀመረው የክትባት ዘመቻ እስከ የካቲት 29 ቀን 2016ዓ.ም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና ለዚሁ ተብለው በተከፈቱ ማዕከላት ይከናወናል ተብሏል።

የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር መከላከያ ክትባቱን የተለያዩ የፀጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች እና ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ስፍራዎች በጤና ተቋማት እና ጊዜያዊ ክትባት መስጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ለመስጠት ከክልሎች እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተነስቷል።

በፍቅርተ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.