Fana: At a Speed of Life!

የማረሚያ ቤቶችን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባዔ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ጉባዔው የማረሚያ ተቋማት ሪፎርም ማስቀጠል፣ የማረም፣ ማነፅና የተሃድሶ ልማት አገልግሎት ውጤታማነት እና የሕግ የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብትና ደህንነት መጠበቅ በሚሉ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል፡፡

በጉባዔው የተገኙት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ÷ በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ የለውጥ ሥራዎች በርካታ ሥር- ነቀል ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ የፍትሕ ዘርፉ መሻሻልን የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመው ÷የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከሚሰሩ የፍትሕ ስርዓት ተቋማት መካከል ማረሚያ ቤት አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በማረሚያ ቤቶች ላይ የመጣውን ውጤታማ ሥራ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው÷ ሁሉም የሕግ ታራሚዎች በተመድ የሕግ ታራሚ አያያዝ መርሆች መሰረት ሰብዓዊ ክብራቸው በመጠበቅ የማረም ማነጽ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ5 ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲወቀስ የነበረው የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ዛሬ የጉባዔ አዘጋጅ መሆኑ የለውጡ ማሳያ ነው ብለዋል።

የጋራ ጉባዔው የልምድ ልውውጥ በማድረግ የሕግ ታሚዎችን በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሐይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይፈጠር ተቀራራቢ አሰራር ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይም ሀገራዊ የማረሚያ ቤት ሪፎርምን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ በማረም፣ ማነጽና ተሃድሶ ልማት ሥራ ሽፋንና ተደራሽነት እንዲሁም በሰው ሃይል ልማት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡

በጀማል አህመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.