በሐረሪ ክልል በኢንቨስትመንት ስም ታጥሮ በቆየ ቦታ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንቨስትመንት ስም ለረጅም አመታት ታጥሮ በቆየ ቦታ እና በሕገ ወጥ የተወረረ መሬት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግስት በሰጠው መግለጫው÷ በህገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብሏል።
የህግ የበላይነትን በማስከበር እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ላይ ማህበረሰቡ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ትምህርት ቤቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የቱሪዝም ስፍራዎችና የአርሶ አደር መሬቶች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ህገ ወጥ የቤት ግንባታዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ህዝቡ ሲጠይቅ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
እንዲሁም በኢንቨስትመንት ተወስደው ለረጅም ጊዜ ታጥሮ የቆየ ቦታ ላይ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁሟል፡፡
አንዳንድ አካላት የክልሉ ልማት ላይ እንቅፋት በመፍጠር እና የመሬት ደላሎችን በማሰማራት የግል ፍላጎታቸውን ሲያስቀድሙ ተስተውለዋልም ነው ያለው በመግለጫው።
በዚህም ያልተገባ ጥቅም እያገኙና የህዝቡንና የክልሉን መንግስት እየጎዱ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ለመፍታት የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱን በመግለጽ፤ ስራውም በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበትና ህብረተሰቡን ያሳተፈ በመሆኑ ውጤት እየተገኘበት ይገኛል ብሏል፡፡
በቀጣይም መሬት አጥረው የያዙና ህግ ወጥ ግንባታ ያከናወኑ ግለሰቦች በፈቃደኝነት እንዲያፈርሱ የክልሉ መንግስት ጥሪ ማቅረቡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በህገ ወጥ አካላት እየተሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስ ክልሉ ለሰላም እና የህግ የበላይነት መከበር ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ ይሆናልም ተብሏል፡፡