ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር ሞሐመድ ሳሌም አልረሺድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ኢመደአ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አቻ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ሞሐመድ በኢመደአ የተሰሩ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶችን መጎብኘታቸውንም የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተቋሙ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች መደነቃቸውንና በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ በታለንት ማዕከል መታገዛቸው ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።