Fana: At a Speed of Life!

ትምህርት ሚኒስቴር 5 የዲጂታል መልቲሚዲያ ስቱዲዮዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ያቋቋማቸውን አምስት የዲጂታል መልቲሚዲያ ስቱዲዮዎች አስመርቋል፡፡

ስቱዲዮዎቹ ሚኒስቴሩ ከማስተርካርድ ፋውዴሽን፣ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና ከሻያሾኔ ተቋማት ጋር በመተባበር ነው የተገነቡት፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የትምህርት ሚኒስትር ተወካይ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና አጋር አካላት ተገኝተዋል።

የዲጂታል መልቲሚዲያ ስቱዲዮዎቹ የዲጂታል መማር ማስተማር ስርዓትን ማጠናከር እንደሚያስችሉ ተመላክቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ተወካይ ሰለሞን አብረሃ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ ስቱዲዮዎቹ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም ዓቀፍ ተደራሽነት፣ የትምህርት ስርዓቱን ለማጠናከር፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመፍጠር ያግዛሉ፡፡

በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ለሥራና ሥራ ፈጠራ የሚያግዛቸውን ክህሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ሰዎች በቦታ ሳይገደቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያስችላሉ ነው ያሉት።

በቀጣይም መሰል ስቱዲዮዎች በአስር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚቋቋሙ ነው የገለጹት፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.