Fana: At a Speed of Life!

በአቶ አባተ አበበ ግድያ ተጠርጣሪ ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ተደራራቢ ክሶች ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል በተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ ተደራራቢ ክሶች ቀረቡበት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ÷ ተስፋዬ ሆርዶፋ ታኅሣስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከምሽቱ 4:00 አባተ አበበ የተባለን ግለሰብ በ3 ጥይት በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎ ማስረጃ በማሰባሰብ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ምርመራ ሲጣራበት መቆየቱን መዘገባችን ይታወሳል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬትም በተጠርጣሪው ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል ማለትም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና የጦር መሳሪያ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ዛሬ ከሰዓት ሁለት ክሶችን መስርቶበታል።

ተከሳሹ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከገላን ከተማ ፈቃድ ካወጣባቸው ስታር እና ማካሮቭ ሁለት ሽጉጦች ውጪ ሌላ ፈቃድ ያልወጣበት ሕገ-ወጥ ሽጉጥ በተሽከርካሪው ደብቆ በመያዝ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በመግደል ሕገ-ወጥ ሽጉጡን ይዞ አምልጦ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጠቅሶ ክስ አቅርቦበታል።

ዐቃቤ ሕግ ከክሱ ጋር የሰው ምስክር ዝርዝርና የተለያዩ የፎረንሲክ ማስረጃዎችንም አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሽም ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰው ከተደረገ በኋላ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የግድያና የከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክሱን በዝርዝር በንባብ ለማሰማት ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.