ጉቦ ሲቀበል ተይዟል የተባለ ዐቃቤ ሕግ ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከግለሰብ ጉቦ ሲቀበል ተይዟል የተባለ የፌዴራል ዐቃቢ ሕግ ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ናሆም ጌታቸው በተባለ ዐቃቤ ሕግ ላይ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 10 (1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የተፈፀመ ጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ በፌደራል ፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በዐቃቤ ሕግነት ተመድቦ በማገልገል ላይ እያለ የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ የግል ተበዳይ አማኑኤል ገነሜ የተባለ ግለሰብ በወንጀል ተጠርጥሮ እና ክስ ተመስርቶ በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ እያለ ተከሳሽ በስራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ በማሰብ “ጉዳዩ በቀላሉ እንዲያልቅለትና ቅጣቱ በገንዘብ መቀጮ እንዲሆን አደርጋለሁ” በማለት የ60 ሺህ ብር ጉቦ እንዲከፍል ተበዳይን በመጠየቅ ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል።
ድርድር ካደረገ በኋላም በጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ሰሜን ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገናኘት 40 ሺህ ብር ለመቀበል በመስማማትና ከተስማሙት ገንዘብ ላይ በተከሳሽ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር በቅድሚያ 10 ሺህ ብር ተላልፎለት የተቀበለ በመሆኑ በቀረበበት ክስ ላይ በዝርዝር ሰፍሯል።
ከዚህም በኋላ ደግሞ በየካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10፡10 አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኝ ካፌ ውስጥ በመገኘት ብር 10 ሺህ ከግለሰብ ተቀብሎ ሲሄድ እጅ ከፍንጅ የተያዘ መሆኑ ተጠቅሶ ጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል ክስ ተከሷል፡፡
ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ገላጭና አስረጂ ማስረጃዎች ተያይዘዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የክሱ ዝርዝር ለተከሳሽ እንዲደርስ በማድረግ ክሱን ለመመልከት ለመጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ