በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።
በአኙዋ ዞን ከአምስቱም ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች የተሳተፉበት ህዝባዊ ውይይት በአቦቦ ከተማ እየተካሄደ ነው።
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በህዝባዊ ውይይቱ ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት÷ የአመለካከትና የጽንፈኝነት ችግሮችን በማስወገድ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል።
በክልሉ የተጀመሩ የጸጥታና የሕግ የበላይነትን የማስፈን ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አስተማማኝ ሰላም ከሌለ ህብረተሰቡ ሰርቶ መግባት ስለማይችል ሁሉም ህብረተሰብ የሰላም እሴቶችን በማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ይበልጥ ውጤት ለማምጣት እንዲተጉም አሳስበዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው÷ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ብዙ እንደሚጠበቅ መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡