Fana: At a Speed of Life!

የተቋም ግንባታ ውጥናችን ስኬታማነቱ የሚረጋገጠው በጠንካራ ሴቶች ወሳኝ ተሳትፎ ነው – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተቋም ግንባታ ውጥናችን ስኬታማነቱ የሚረጋገጠው በጠንካራ ሴት የሰራዊት አባላት ወሳኝ ተሳትፎ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “የሴቶች ተጋድሎ ለሰላም እና ለፍትሕ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።

ሌ/ጀ ይልማ መርዳሳ በዚህ ወቅት÷ በዓድዋ አርበኛዋ እቴጌ ጣይቱ፣ በሴት አውሮፕላን አብራሪዋ ሙሉ እመቤትና በሌሎች ሴት ጀግኖቻችን ታሪካዊ ተጋድሎ የኢትዮጵያ ክብር ከፍ ማለቱን አውስተዋል።

የተቋም ግንባታ ውጥናችን ስኬታማነቱ የሚረጋገጠው በጠንካራ ሴቶች ወሳኝ ተሳትፎ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በአየር ሃይል ደረጃ ሴቶችን ለማብቃት እና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሰፋፊ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ልዩ ስታፎች ጉዳይ ዘርፍ ሜ/ጄ ጥሩዬ አሰፌ በበኩላቸው÷ ከለውጡ ወዲህ ሴቶችን ወደ ሃላፊነት ለማምጣትና በየተመደቡበት ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ የተደረገው ድጋፍ አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም አንዷ እማኝ እሳቸው እንደሆኑ ገልፀው÷ ለዚህ የበቁትም በይቻላል መንፈስ ጠንክሮ በመስራት እንደሆነም አብራርተዋል።

ተቋሙን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እያገለገሉ ያሉ ሴቶች ወቅቱ በሚጠይቀው የተወዳዳሪነት መንፈስ ዝግጁነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በዕለቱ በስራ አፈፃፀማቸው ውጤታማ ለሆኑ ሴት የሰራዊት አባላት የምስጋና ምስክር ወረቀት መበርከቱንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.