Fana: At a Speed of Life!

56 የይግባኝ አቤቱታ መዝገቦች ለምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ እንደሚቀርቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 56 የይግባኝ አቤቱታ መዝገቦች ለፌዴሬሽን ም/ቤት መደበኛ ጉባዔ እንደሚቀርቡ የም/ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የቀረቡለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎች ላይ ምርመራ አካሂዷል፡፡

በዚህም ቋሚ ኮሚቴው የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ 6 መዝገቦች እና 2 ለተጨማሪ ጥናትና ምርመራ በይደር የቆዩ እና በይግባኝ ለምክር ቤቱ የቀረቡ መዝገቦች ለም/ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ለውሳኔ እንዲቀርቡ ወስኗል፡፡

ከዚህ ባለፈም 56 መዝገቦች በዝርዝር በመመርመር የውሳኔ ሃሳብ ተዘጋጅቶላቸው ለም/ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ለውሳኔ እንዲቀርቡ መወሰኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለምክር ቤቱ ያቀረባቸውን የሕገ መንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሃሳቦች እና በይግባኝ ለምክር ቤቱ የቀረቡ ጉዳዮችን በመመርመር ለም/ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ጠቅሰዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ካቋቋማቸው አራት ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል የሕገ መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ አንዱ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታዎችን ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳቦችን ለም/ቤቱ እንደሚያቀርብም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.