Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ “ደህንነቱ ለተጠበቀ ነገ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ኃይል ትብብር” በሚል መሪ ሀሳብ በዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑክ በፈረንጆቹ ከመጋቢት 5 እስከ 7 ቀን  2024 በዱባይ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ልዑካን ቡድኑ በቦታው ሲደርስ በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ቆንሰላ ጀነራል ፅ/ቤትና በአቡዳቢ የኢፌዲሪ ኤምባሲ አቀባበል ተደርጎለታል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ከዱባይ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሌተና ጀነራል አብዱላህ ከሊፋ አል ማሪ ጋር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጎንዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም የሀገራቱን ግንኙነት በፖሊስ ዘርፍ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ አመራሮቹ በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ ልውውጥ፣ በቪአይፒ ጥበቃ፣ በአቪዬሺን ደኅንነት፣ በፈንጂ ቁጥጥርና በሁነት ደኅንነትና በሎጂስቲክ ድጋፍ በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም በዱባይ ኢንተርነት ሲቲ ሞቶሮላ ማዕከል ቴክኒካል ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ሙያተኞችን ጎብኝተዋል፡፡

ስልጠናውን እየሰጡ ካሉ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሞቶሮላ ሶሉሺን ዳይሬክተር ዩቫል ሀናን እና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የሞቶሮላ ሲስተም ኢንጂነር ሙሉጌታ መለሰ ጋርም ተወያይተዋል፡፡

በዱባይ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ በሽብርተኝነት፣ በኢኮኖሚ ወንጀሎች፣ በህገ-ወጥ የገንዘብና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ በሳይበር ወንጀል፣ በትራፊክ ደህንነትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክክር መካሄዱን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.