Fana: At a Speed of Life!

ሴቶች የስልጣን ጠረጴዛ ላይ ካልደረሱ ሙሉ ፍትሕና ዴሞክራሲ አለ አይባልም- ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመሰረታዊነት ሴቶች የስልጣን ጠረጴዛ ላይ ካልደረሱ ሙሉ ፍትሕ፣ ሙሉ ሰላም እና ሙሉ ዴሞክራሲ አለ ለማለት ያስቸግራል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ በዓለም ለ113ኛ እና በኢትዮጵያ ለ48ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በኢትዮጵያ የሴቶች ቀን መከበር ሲጀምር ምንም እንኳን ብዙ መተግበር የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩም ሴቶች ለራሳቸው ጊዜ ሰጥተው ሰብሰብ ብለው መነጋገር የሚችሉበት ዕድል የፈጠረ ነበር ብለዋል፡፡

ሂደቱ ቀጥሎም ከ40 ዓመታት በኋላ ብዙ ለውጦች ታይተዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ ዛሬ ላይ የእሳቸው የሀገር ፕሬዚዳንትነት ደረጃ ላይ መድረስ የዛ ለውጥ አካል እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የብዙ ሴት ሚኒስትሮች መምጣት እና የመዲናዋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሴት መሆናቸው የትግሉ ውጤት ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሀገሪቱ በዚህ ደረጃ የሴቶች ለስልጣንና ለአመራርነት መብቃት በችሮታ የተሰጠ ሳይሆን የመስራት አቅማችውን አሳይተውና አስመስክረው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለውጡ መድረስ ያለበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰና ለዚህም ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሴቶች በዓለም ዙሪያ ሀገራቸውን በሰፊው እንዳስተዋወቁ አንስተው አሁንም የተለየ መብት እንዲሰጣቸው ሳይሆን እኩል መብት እንዲሰጣቸው እንደሚጠይቁ ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም ስልጣን ዋናው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ በማንሳት ጉድለቶችን ሁሉ ከፍ ብሎ ለመመልከት የሚቻለው ስልጣን ላይ ሲደረስ ነው ብለዋል፡፡

ሴቶችን ማብቃት በከተማ ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ በገጠር የሚገኙ ሴቶችም በየዘርፉ ማደግ እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት፡፡

ለዚህም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በግብርና እና በትምህርት የተያዙ የልማት ፕሮግራሞች በዋነኛነት በገጠር ያሉ ሴቶችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ መሪ ሀሳብ “ትምህርት ለሁሉም” የሚል በመሆኑ ከምንም በላይ ትምህርትን ለሴቶች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ተረባርቦ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ ሴቶችን አሰባስቦ በአንድ ካምፕ ውስጥ አስጠልሎ፣ መግቦ እና አሰልጥኖ በስራ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የተያዘውን ፕሮጀክት አድንቀዋል፡፡

ይህን መሰል ተሞክሮ በየክልሉ ሊተገበር እንደሚገባና ማድረግ እንደሚቻልም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይም በሴቶች ላይ የሚደርስን የትኛውንም ዓይነት አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጥቃት ማውገዝና መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.