Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን እና ጂቡቲን ግንኙነት በይበልጥ ለማሣደግ ቁርጠኛ ነው- አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ እና ጂቡቲን ግንኙነት እና ትብብር በይበልጥ ለማሣደግ ቁርጠኛ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በጂቡቲው ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ) 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ ብልጽግና ፓርቲ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍና ቀልጣፋ አገልግሎት እውቅና ይሰጣል ብለዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲም የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ግንኙነት በዓርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን እንደሚገነዘብ ጠቅሰዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ሊቀ-መንበር አቶ ኢስማኤል ኡማር ጌሌህ እና የጂቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

የተከበሩ አብዱል ቃድር ካሚል መሐመድ የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ምክትል ሊቀ-መንበር እና የጂቡቲ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር

የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ዋና ጸሐፊ እና የጂቡቲ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ዳዋሌ
የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) አመራር እና አባላት፣ የክብር እንግዶች፣ ክቡራትና ክቡራን

ብልጽግና ፓርቲን በመወከል የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) 45ኛ የምስረታ በዓል ላይ መገኘቴ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ለጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ።

በእኩልነት፣ በፍትሕ፣ በመከባበር እና በብልጽግና ላይ የተመሰረተ የብልጽግና ፓርቲን በኢትዮጵያ ውስጥ የምንወክል ልዑካን ነን። በዚህ ዝግጅት ላይ እንድንሳተፍ ስለጋበዛችሁን እናመሰግናለን። በክብር እና በወንድማማችነት ለልዑካኖቻችን ላደረጋችሁት መልካም አቀባበልም እናመሰግናለን።

የተከበሩ ፕሬዚዳንት፣ ክቡራን እና ክብራት

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ሞቅ ያለ ሰላምታዬን እና የእንኳን አደረሳችሁን እንድትቀበሉ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

የተከበሩ ፕሬዚዳንት
ክቡራን እና ክብራት

ከጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ታሪክ እንደምንረዳው ያለፉት 45 ዓመታት ከጎረቤት ሀገራትና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለእድገት፣ ለሰላም፣ ለህዝቦች አንድነት፣ አብሮነት እና ትብብር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ወቅት ነው።

በፕሬዚዳንት ኢስማኢል የሚመራው የጂቡቲ አመራር ያላሰለሰ ጥረት ውጤት እያሳየ መሆኑን እና ጂቡቲን ጠቃሚ የንግድ ማዕከል እንድትሆን፣ የመረጋጋት ምሳሌ እና የእድገት ጎዳና እንድትሆን እንዳደረጋት በልበ ሙሉነት እንመሰክራለን።

በጂቡቲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ለአፍሪካ ቀንድ ውህደት እና የጋራ ተጠቃሚነት የተሰሩ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እናደንቃለን። በአበይትነት ጂቡቲንና ኢትዮጵያን የሚያገናኙት ወደቦች፣ የባቡር መስመር እና አውራ ጎዳናዎች መጥቀስ ይቻላል።

የተከበሩ ፕሬዚዳንት
ክቡራን እና ኩቡራት

በአሁኑ ወቅት ከ14 ሚሊየን በላይ አባላት ያሉት ብልጽግና ፓርቲ ለጎረቤት ሀገራት በዲፕሎማሲ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና በአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች መካከል ያለውን ውህደት እና የጋራ ተጠቃሚነት ለማጠናከር በፕሮግራሙ ላይ በግልፅ አስቀምጧል።

ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞች እርስ በርስ የተያያዙ እና የማይነጣጠሉ ናቸው ብሎ ያምናል። ትብብራቸውም የተቀደሰ ነው ብሎ ያምናል።

ብልጽግና ፓርቲ ለጅቡቲ ጠቃሚ የሆነው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሶማሊያ አስፈላጊ እንደሆነ ለጎረቤት አገሮች ጠቃሚ የሆነው ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። የኢትዮጵያ ጥቅም ለሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ይገነዘባል።

በተለይ ብልጽግና ፓርቲ ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍና ቀልጣፋ አገልግሎት እውቅና ይሰጣል። ብልጽግና ፓርቲ የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ደህንነት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ግንኙነት በአርአያነት የሚጠቀስ እና በሁለቱ ሀገራት መንግስታት እና መሪዎች ላይ በተደረጉ ለውጦች ተጎድቶ አያውቅም ብሎ ያምናል።

ብልጽግና ፓርቲ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እና ትብብር ሁሌም ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው። በመሆኑም የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች መልካም ጉርብትና፣ ወንድማማችነት፣ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የተሳኩና ውጤታማ እንዲሆኑ የሁለቱ ፓርቲዎች ግንኙነትና ትብብር እንዲጠናከር ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተከበሩ ፕሬዚዳንት
ክቡራን እና ክቡራት

ባለፉት አመታት በጋራ ያስመዘገብናቸው ድሎች ውጤቶች ተባብረን በኛም ሆነ በአለም ላይ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ማሸነፍ ይጠበቅብናል።

አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን፣ ሽብርተኝነትን እና ሌሎች የደህንነት ስጋቶችን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ሃብት መመናመንን፣ የቴክኖሎጂ ስጋቶችን እና መርህ የለሽ ጣልቃገብነት በትብብር መታገል አለብን።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጽናትን የሚጠይቅ ሲሆን አንድ በሚያደርገን መርሆዎች እና እሴቶች ማለትም ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ የህዝብን ጥቅም መደገፍ፣ ወንድማማችነት መተባበር፣ ፈጠራን ማጎልበት እና ሀብታችንን በጋራ መጠቀም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር እንደ ውሃ፣ መብራት፣ የተለያዩ ምርቶች ወዘተ ያሉትን ሃብቶቿን እንደምታጠናክር አረጋግጣለሁ።

የተከበሩ ፕሬዚዳንት
ክቡራን እና ክቡራት

ንግግሬን የምቋጨው የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ህልውና ወቅት ያጋጠሙትን መልካም ነገሮችና ተግዳሮቶች እንወቅ ከዚሁ ጎን ለጎንም ያሉትን እድሎች በመጠቀምና ብሩህ ተስፋን ለመፍጠር ትኩረት እንስጥ ለማለት እወዳለሁ።

ብልጽግና ፓርቲ ለጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) እና ለጅቡቲ ህዝቦች እድገት፣ ልማት፣ አንድነት እና ብልጽግና ይመኛል።

ብልጽግና ፓርቲ ከእውነተኛ ድጋፍ ጋር ሁሌም ከጎናችሁ እንደሚቆም፣ ለጋራ አላማችንና ራዕያችንም ከጎናችሁ እንደሚቆም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

የጂቡቲ ገዥ ፓርቲ (አር ፒ ፒ ) ለዘላለም ይኑር!

ጅቡቲ ለዘላለም ትኑር!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

በሁለቱ ሀገራት መካከል አርአያነት ያለው ግንኙነት ለዘላለም ይኑር ከፍም ይበል!!

አመሰግናለሁ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.