የፓፓያ ምርጥ ዘር ችግኝ የማስፋፋት ንቅናቄ ባለፈው ዓመት 10 ሺህ 400 ሄክታር ደርሷል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓፓያ ምርጥ ዘር ችግኝ የማስፋፋት ንቅናቄ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ባለፈው ዓመት 10 ሺህ 400 ሄክታር መሬት መድረሱን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለውጭ ገበያ የሚውሉ የፍራፍሬ ምርቶችን በብዛትና በጥራት የማምረት ስራው በፍጥነት በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።
የዛሬ ሶስት ዓመት የተጀመረው የፓፓያ ምርጥ ዘር ችግኝ የማስፋፋት ንቅናቄ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ ባለፈው ዓመት 10 ሺህ 400 ሄክታር መሬት መድረሱን አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት 50 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር የፓፓያ ችግኝ ለማልማት “የቁጭት ዕቅድ” መያዙን ጠቅሰው፤ ለዚህም 135 ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
እስከ አሁን 127 ሚሊዮን ችግኝ በማዘጋጀት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለው ቀሪ ጊዜ ዕቅዱ በሙሉ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።