Fana: At a Speed of Life!

የ3 ሐይቆች ከ978 ሔክታር የሚልቅ አካል ከእንቦጭ ነጻ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዝዋይ፣ አባያ እና ጫሞ ሐይቆች 978 ነጥብ 45 ሔክታር ከእንቦጭ ነጻ መደረጉን የስምጥ ሸለቆ ቤዚን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዴቢሶ ዴዴ ገለጹ፡፡

በ2016 ዓ.ም ከዝዋይ ሐይቅ 1 ሺህ 470 ሔክታር፣ ከአባያ ሐይቅ 7 ሺህ 810 ሔክታር እና ከጫሞ ሐይቅ 25 ሔክታር እንቦጭ ለማስወገድ መታቀዱንም አስታውሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከዝዋይ ሐይቅ 120 ሔክታር ለማስወገድ ታቅዶ 240 ሔክታር ከእንቦጭ ነጻ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ከአባያ ሐይቅ 1 ሺህ 540 ሔክታር ከእንቦጭ ነጻ ለማድረግ ታቅዶ በተከናወነው ሥራ 725 ነጥብ 2 ሔክታሩን ማሳካት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ከጫሞ ሐይቅም 12 ሔክታር እንቦጭ ለማስወገድ ታቅዶ 13 ነጥብ 25 ሔክታር የሐይቁ አካል ከአረሙ ነጻ መሆኑን ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡

እንቦጩን የማስወገዱ ሥራ የተሠራው÷ የመንግስት ተቋማትን፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን፣ ዓሣ አስጋሪ ማኅበራትንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ነው ብለዋል፡፡

የሚመለከታቸው ተቋማት ተሳትፎ እና የጥናትና ምርምር ሥራዎች ውስን መሆን፣ የሎጅስቲክስ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን አለመሆን አረሙን በማስወገድ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.