የዲፕሎማሲ ስራን በጥበብና በእውቀት ማከናወን እንደሚገባ አምባሳደር ታዬ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርካታ ለውጦች ውስጥ እያለፈ ያለውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ባገናዘበ መንገድ በጥበብ እና በእውቀት የዲፕሎማሲ ሥራን ማከናወን እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አስገነዘቡ፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር የትውውቅ እና የውይይት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
አምባሳደር ታዬ በወቅቱ÷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተቋም ደረጃ ምን መምሰል እንዳለበት፣ የተቋሙ ባለሞያዎች አቅም እና ችሎታ፣ እንዲሁም የተቋሙ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አመላካች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በየጊዜው የሚለዋወጠውን የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ከግንዛቤ በማስገባት ራሳቸውን በሁሉም ዘርፍ በማብቃት መትጋት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው÷ አምባሳደር ታዬ በተቋሙ ውስጥ ያለፉ እና በሚገባ የሚያውቁት በመሆናቸው ተቋሙን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር አበርክቶ እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
ሁሉም ባለሙያ በሙሉ አቅሙ መስራት እንዳለበትም መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።