Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት አነሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ያነሳው በ17ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ነው።

ምክር ቤቱ የአባሉን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት ተነስቶ ክስ ማቅረብ እንዲቻል ጥያቄ ያቀረቡት የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)÷ አባሉ መንግስታዊ ስርዓትን በሃይል ለመናድ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀስ ቡድን መመሪያ ሲሰጡ እንደነበር ገልጸዋል።

“የምክር ቤት አባሉ ለእስር ከተዳረጉ ከሰባት ወራት በላይ ተቆጥረው ሳለ፣ አሁን ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳት ለምን አስፈለገ”? የሚሉ ጥያቄዎችን የምክር ቤት አባላት አንስተዋል፡፡

“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ መደበኛው የዳኝነት ሂደት ጣልቃ መግባት እንደማይችል እየታወቀ፣ ሂደቱን መከወን ለምን አስፈለገ” የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

ምክር ቤቱም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ካደመጠ በኋላ፣ በሁለት ተቃውሞና በሁለት ድምፀ ታቅቦ የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምፅ አንስቷል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ በስብስባው ዘጠኝ ረቂቅ አዋጆችን እንደሚያጸድቅ እና ሁለት ረቂቅ አዋጆችን ደግሞ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች እንደሚመራም ይጠበቃል።

በበርናባስ ተስፋየ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.