ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስከብር መልኩ ትሰራለች- ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስከብርና በሚያስቀጥል መልኩ እንደምትሰራ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የተሾሙ የ11 ሀገራትን አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል፡፡
አምባሳደሮቹ ከእስያ ሶስት ሀገራት፣ ከአፍሪካ አምስት ሀገራት እንዲሁም ከአውሮፓ ሶስት ሀገራት በኢትዮጵያ የተሾሙ ናቸው።
የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንቷ ያቀረቡት የኬንያ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ማላዊ፣ ኳታር፣ ጃፓን፣ አዘርባጃን፣ ስፔን፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና አርሜንያ ተወካዮች አምባሳደሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ከሁሉም አምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ፥ ኢትዮጵያ ከየሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሸ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስከብርና በሚያስቀጥል መልኩ እንደምትሰራም ነው የገለጹት።
አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።