Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ አስችሏል – አቶ ገብረመስቀል ጫላ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ ማስቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ኮንትሮባንድ የገቢና የወጪ ንግድ ሥርዓትን በማቀጨጭ የሀገሪቱ ቁልፍ ችግር ሆኗል ብለዋል።

በተለይም ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በቁም እንስሳት፣ በጫት፣ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላይ የሚያካሂዱት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በወጪ ንግድ ሥርዓቱ ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮንትሮባንድ የተሰማሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሀገርንና ህዝብን የሚጎዱ ድርጊቶች እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮንትሮባንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁልፍ ችግር ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠርም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የጸጥታና ጉምሩክ ተቋማት ግብረ ሃይል ተደራጅቶ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ በመሆኑ ሙሉ ቦቴ ጭምር ወደ ጎረቤት ሀገራት ሄዶ የሚሸጥበትና ኢትዮጵያም ስትፈተንበት የቆየችው ጉዳይ እንደነበር አስታውሰዋል።

ቀስ በቀስ በተካሄደ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ከጎረቤት ሀገራት ተመሳሳይ እንዲሆን በማድረግ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ እንደተደረገ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አሁንም በነዳጅ ላይ የተወሰነ የኮንትሮባንድ ዝንባሌ ቢስተዋልም በተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ከሀገር የሚወጣበት ሥርዓት እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም የነዳጅ አቅርቦትን በዘመናዊ መልኩ ለማስተዳደር ከመነሻው እስከ ስርጭት ሂደቱ በኦንላይን ሥርዓት ለመከታተል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት የሚሳተፉበትን ምኅዳር ለመፍጠር እየተሰራ ነውም ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.