Fana: At a Speed of Life!

ህዝባዊ መድረኮች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠትና ለግጭት አፈታት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝባዊ መድረኮች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት፣ የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማጣጣም እና ለግጭት አፈታት አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄድ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች ውስጥ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

ህዝባዊ የውይይት መድረኮች የሚታዩ ችግሮችን መነሻዎች፣ መንስኤዎች እና መፍትሔዎቻቸዉ ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤን ያሳድጋሉ፣ የተለያዩ ወገኖች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹና ድምጻቸዉ ለማሰማት ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት፣ የተለያዩ ፍላጎቶችን ለመጣጣምና ግጭት ለመፍታት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

አሳታፊ፣ አካታች እና የተለያዩ አመለካከት የሚራመድባቸው የውይይት መድረኮች ህብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ አብሮነት እና ትብብርን በማጎልበት መተማመንን እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

መተማመን ከተፈጠረ ለሀገረ መንግስቱት ሆነ ለሀገር ግንባታ ሂደት ዘላቂ መሰረት እንደሚሆን አመላክተዋል።

ህዝባዊ ውይይቶች የተለያዩ ማህበረሰቦች በዉስጣቸዉ ያለዉን ውጥረት እንዲያረግቡ፣ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ እና በሰላም አብሮ ለመኖር እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያካሄዷቸው እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሀገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ያደረጓቸው ዉይይቶችም በዚሁ መርህ መሰረት የተደረጉ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከ70 በላይ በሆኑ ከተሞች የተካሄዱት ህዝባዊ የዉይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አንስተው፤ በውይይቱ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በጋራ ጉዳዮች ለመወያያት የነበረዉ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ ጥያቄዎቹን ሚዛናዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ያነሳበት፣ የተሰሩ ስራዎችን እዉቅና የሰጠበትና ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ ፍላጎቱን የገለጸበት፣ መሪዎችንም ያበረታታበት፣ ጉድለቶችንም መንግስት እንዲያርም በነፃነት ስሜት ያነሳበት ነበር ብለዋል።

የተጀመሩ የለዉጥ ስራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ፍላጎቱን የገለፀበት፣ ህዝቡ ለሰላሙም ሆነ ለልማቱ ከፍተኛዉን ድርሻ በመወጣት ከእዳ ወደ ምንዳ ለመቀየር በከፍተኛ ተነሳሽነት እና በቁጭት ለመስራት፣ ሀብት ለመፍጠር እና የወል ትርክት ላይ በማተኮር ህብረብሄራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ዝግጁነቱን ያረጋጋጠበት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከፍተኛ አመራሩም የህዝቡን የማልማት ፍላጎቶች እና እንዲቀረፉ የሚፈልጋቸዉን መሰረታዊ ጉዳዮች ለመረዳት ብሎም ተገቢዉን ልምድ እና ግንዛቤ የፈጠረለት እንደሆነ አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ከሰላምና መረጋጋት፣ ከኑሮ ዉድነት የስራ እድል ፈጠራ፣ ከመሰረተ ልማቶች አቅርቦቶች እና ሌሎች የልማት ስራዎች እና አካባቢያዊ ጉዳዮችን በስፋት ያነሳበትና ችግሮቹን በቅንጅት ለመፍታት መግባባት የተፈጠረበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዕቅድ የተያዙ፣ በቂ በጀትም የተመደበለቸዉ እና በአስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት በወጉ ያልተፈጸሙ የልማት ስራዎች በቅደም ተከተል መፍታት እንደሚገባ የገለጹት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ከዘላቂ እና አዎንታዊ ሰላም፣ ህግ ማስከበር ብሎም ሕገ ወጥነትን መከለካል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የተነሱ ጉዳዮችን አሰራሮችን በማዘመን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለዉጥ ማምጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ለሀገረ-መንግስቱ ቀጣይነት ያለውን ዝግጁነቱን እና ቁርጠኛ አቋም ያንጸባረቀባቸው እንዲህ አይነቶቹ መድረኮች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.