በሀሰተኛ ሰነድ 300 ካሬ ሜትር ይዞታ ወስዶ ሸጧል የተባለው ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀሰተኛ ሰነድ አርሶ አደር ነኝ በማለት 300 ካሬ ሜትር ይዞታ ወስዶ ሸጧል የተባለው የቴክኒክ ባለሙያና ግብረ አበሩ ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ፤ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አቅርቦባቸዋል።
ክሱ የቀረበባቸው ከሳሾች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቴክኒክ ጉዳዮች አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ የነበረች እህተማርያም መላኩ ፀጋዬ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቴክኒክ ባለሙያ የነበረው ተስፋዬ እጀታ ዲማ ናቸው።
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዚህም በአንደኛ ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ በአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቴክኒክ አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ ሆና በምትሰራበት ወቅት ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ 2ኛ ተከሳሽ አርሶ አደር ሳይሆን ሀሰተኛ የአርሶ አደር ኮሚቴ አባላት እንደሆነ በማስመሰል ሀሰተኛ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የእርሻ ስራ ግብር ደረሰኝ በማዘጋጀት፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 2 አስተዳደር ጽ/ቤት ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ሳይላክ እንደተላከ በማስመሰል በክ/ከተማው መሬት አስተዳደር ማህደር እንዲዘጋጅለት በማድረግ 2ኛ ተከሳሽ ምንም አይነት ቤት ሳይኖረው ቤት እንዳለው በማስመሰል በይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ ንድፍ እንዲዘጋጅለት ተደርጓል።
በዚህ መልኩ አንደኛ ተከሳሽ ሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 02 ውስጥ ጠቅላላ የሊዝ ጨረታ ዋጋው 6 ሚሊየን 301 ሺህ 638 ብር የሆነ አጠቃላይ 300 ካሬ ሜትር ይዞታን ሁለተኛ ተከሳሽ እንዲወስድ በማድረግ በዋና እና ልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ የመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ በሁለቱም ግለሰቦች ላይ ቀርቧል።
በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ በቀረበ ክስ ደግሞ ተከሳሹ አርሶ አደር ሳይሆን አርሶ አደር እንደሆነ በማስመሰል ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በህገ ወጥ መንገድ ሀሰተኛ ሰነዶችን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 02 የ300 ካሬ ሜትር ይዞታ ከወሰደ በኋላ የንብረቱን ህገወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን በማሰብ ንብረቱን አቶ አለማየሁ ለሚ ለተባለ ግለሰብ ነሃሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በተደረገ ውል በ1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በሽያጭ ያስተላለፈ መሆኑ ተጠቅሶ በፈፀመው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡
2ኛ ተከሳሽ ዛሬ ችሎት ቀርቦ ክሱ እንዲደርሰው ከተደረገና በንባብ ከተሰማ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች እንዲሰሙለት መጠየቁን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመጠባበቅና እና አንደኛ ተከሳሽ በመጥሪያ እንድትቀርብ በማዘዝ ለመጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ