ቢዝነስ

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጭ ገበያ ካቀረባቸው ምርቶች 20 ሚሊየን ዶላር ገቢ አገኘ

By Feven Bishaw

March 19, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 20 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ እንደገለጹት÷ በ2016 በጀት ዓመት ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች በፓርኩ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ የንቅናቄ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም 22 ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች በፓርኩ ለመሰማራት ውል መፈጸማቸውንና ከእነዚህ መካከልም 19ኙ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በፓርኩ ወደ ስራ ከገቡት መካከል በአውሮፓና አፍሪካ ገበያ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት እንደሚገኙበትም ነው የጠቆሙት።

በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች 44 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት 20 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከትላልቅ ተቋማት ልምድ በመቅሰም የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተከናውኗል ብለዋል።