የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የድጋፍና ክትትል ልዑክ በአማራ፣ በሶማሌ፣አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው፡፡
በዚሁ መሠረትም÷ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በደሴ ከተማ አሥተዳደር የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን እየጎበኘ ነው፡፡
በሌላ በኩል በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገ/መስቀል ጫላ የተመራ ልዑክ በተገኘበት በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን አቦቦ ወረዳ የተፋሰስ ልማትን ማጠናከር የሚያስችል የንቅናቄ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷በክልሉ የግብርና ልማትን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፋሰስ ልማት ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተመሳሳይ በሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ ልዑክ በድሬዳዋ የገጠር ወረዳዎች የሥራ ጉብኝት አካሂዷል፡፡
እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በሶማሌ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ ከተሞች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እና የኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በጉብኝቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
እንዲሁም በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ ከተማ በቴክኖሎጂ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን፣ የከተማ ግብርና፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ ተቋማት ሥራዎችን መመልከቱን የአሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በከድር መሀመድ