Fana: At a Speed of Life!

የሽግግር ፍትህ ብቁ የሰውሃይል የያዘ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓትን ለመገንባት ያስችላል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በሽግግር ፍትህ ሪፎርም ተግዳሮቶች ዙሪያ ከክልሉ ከፍተኛ የፍትህ ተቋማት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ርዕሰ መስተደዳሩ በውይይቱ እንደገለጹት÷ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ የሽግግር ፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉ ነው።

የሽግግር ፍትህ ሪፎርም ዕውቀትና ሥነ ምግባር የተላበሰ የሰው ሃይል የያዘ ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት በክልሉ ማስፈን የሚያስችል ፖሊሲ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከፍትህ አንጻር ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም አንዳንድ የሚታዩ ተግዳሮቶች እንዳሉ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ሀገራዊ የሽግግር ፍትህ ሪፎርም ፖሊስ በክልሉ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ አመራሮች በቁርጠኝነት መስራት እና ሒደቱን መምራት እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።

ጠንካራ የፍትሕ ተቋማት እንዲኖሩና ነጻነታቸውን እና ገለልተኝነታቸውን እንደጠበቁ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ እምነት የሚጣልበት ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት ለመገንባት መሰራት ያለባቸውን በመለየት ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.