ለዘንድሮ የሐጂ ጉዞ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ሁጃጆች ተመዝገበዋል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዘንድሮ የሐጂ ጉዞ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ሁጃጆች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት አስታወቀ።
የ1 ሺህ 445ኛው የሐጂ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመከናወን ላይ ሲሆን÷ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የሐጅና ኡምራ ዘርፍ ኃላፊ ሸህ አብዱልአዚዝ መሃመድ÷ ዘንድሮ የምዝገባና ሌሎችም አገልግሎቶች በተቀላጠፈ መልኩ እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለሐጅና ኡምራ ተጓዦች ቀደም ሲል የነበሩትን 18 የምዝገባ ጣቢያዎች ወደ 27 በማሳደግ በየአቅራቢያው አገልገሎት የሚሰጥበት አሰራር ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በዚህም ለመመዝገብ ከታቀደው 12 ሺህ እስካሁን 10 ሺህ 100 ሁጃጆችን መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው÷ በቀሪ ቀናት ሌሎችም አገልግሎት ፈላጊዎች መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁጃጆች የሐጅ ሥነ ስርዓት ፈጽመው እስኪመለሱ ድረስ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ መረጃ የሚሰጡ የዲጂታል አገልገሎቶች እንደተጀመሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡