በሚቀጥሉት 11 ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንደሚጠናከሩ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት11 ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
አብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይና ተጠቃሚ ቦታዎች በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ እንደሚስተዋልባቸውም ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ፣ በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ በትንበያው ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ፣ የመካከለኛው እና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የዋግህምራ ዞኖች፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ እንዲሁም የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን÷ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የአፋር ክልል ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ የምስራቅ፣ የመካከለኛው እና የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ ከሱማሌ ክልል የሲቲ፣ የፋፈን፤ ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፤ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፤ ከትግራይ ክልል የምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ ከሶማሌ ክልል የዳዋ፣ የሊበን፣ የአፍዴር፣ የኤረር እና የነጎብ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል በጋምቤላ፣ ቋራ፣ መተማ፣ መተራ፣ ዱብቲ፣ ሎጊያ፣ አብዓላ፣ አፍዴራ፣ ጎዴ፣ ቀብሪ ደሃር እና ደጋሀቡር ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ35 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
ሁኔታው ለበልግ እርሻ ሥራ፣ ለአፈር እርጥበት መሻሻል ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት፣ የረጅም ጊዜ ሰብሎችን አስቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች የማሳ ዝግጅት ለማከናውን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንፃር ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡