Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ስደተኞችንና አስተናጋጅ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 2ኛ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና የአስተናጋጅ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

የፕሮጀክቱ ትግበራ የኔዘርላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እና ሌሎች የሰብአዊና የልማት ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ትግበራ በፈረንጆቹ ከ2020 እስከ 2023 የተከናወነ ሲሆን÷ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።

በዚህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የአስተናጋጅ ማኅበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር÷በፕሮጀክቱ ስደተኞችና ተቀባይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የትምህርት የሙያ ሥልጠና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ድጋፍና እገዛዎች የሚደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራትን ስደተኞች ተቀብላ ማስተናገዷን አድንቀው÷ለዚህ ደግሞ ኔዘርላንድ እገዛ እንደምታደርግ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን÷ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገራትን ስደተኞች ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ስደተኞችን ያሳተፈ የምጣኔ ኃብትና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ልማት በመተግበር ላይ ይገኛልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.