በሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) የተመራ የልዑካን ቡድን በኦሮሚያ ክልል የልማት ስራዎችን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) የተመራው የልዑካን ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደደር እና ጎሮጉቱ ወረዳዎች ተዘዋውሮ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
በጎሮጉቱ ወረዳ በሮዳ ከተማ ለወላጅ አልባ ህፃናት የተገነባው የመኖሪያ ቤት በልዑካን ቡድኑ ተጎብኝቷል።
ህፃናት ከሚኖሩበት ቤት በተጨማሪ ህይወታቸውን ለመምራት ይቻል ዘንድ ለኪራይ የሚሆን እና 1 ሺህ 500 ብር የገቢ ምንጭ ያለው ተጨማሪ ክፍል ግንባታና እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎች ክፍል ጋር ተገንብቶ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መደረጉም ነው የተነገረው፡፡
ይህ ተግባር በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት ሰው ተኮር መሆኑን እስከታች ድረስ የተንፀባረቀበት ነው ሲልም ፓርቲው በማህበራዊ ትስስር ገጹ አመልክቷል፡፡
በከተማዋ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት እምነት አባቶች ብቻ በአንድ ላይ ተባብረው ትምህርት ቤት ገንብተው ማስረከባቸው ሌላው የመቻቻል ምልክት ሆኗልም ነው የተባለው።
ይህም ሁኔታ ለዞኑ ሁለንተናዊ ሠላምና ልማት ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ቡድኑ መታዘብ ችሏል ተብሏል::