Fana: At a Speed of Life!

በሚኒስትሮች የተመሩ የተለያዩ ልዑኮች የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የተመሩ የተለያዩ የድጋፍ እና ክትትል ልዑካን ቡድኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው፡፡

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን እና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዱራሜ ካምፓስ የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትጋት መሥራት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በዞኑ ዳምቦያ ወረዳ የታዩት የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በመጥቀስ በአንዱ አካባቢ ያለውን ተሞክሮ ወደ ሌላው ማስፋፋት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የተመራ ልዑክ በጋምቤላ ከተማ በእንስሣት እርባታ ላይ የተሰማሩ አርብቶ አደሮችን ሥራ ተመልክቷል።

በጉብኝቱ ላይም አርብቶ አደሩ ከባህላዊ የእርባታ ዘዴ ወጥቶ በዘመናዊ መንገድ መሥራት እንደሚጠበቅበት የተገለጸ ሲሆን÷ በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎችም ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡

እንዲሁም በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በምዕራብ አርሲ ዞን ነጌሌ አርሲ ወረዳ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችን፣ የበጋ ስንዴ ልማት፣ የከብት እርባታ፣ የዜግነት አገልገሎትን ጨምሮ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.