የሀገር ውስጥ የምግብ ምርትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስርአተ-ምግብን ለማሻሻል የሀገር ውስጥ የምግብ ምርትን ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከቺልድረንስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (ሲፍ) ዳይሬክተር እና ልዑካን ቡድኑ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ÷ ሲፍ በኢትዮጵያ እየተገበራቸው ስለሚገኙ ፕሮጀክቶች እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰሩ ስለሚገኙ ተግባራት ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
አሁን ላይ በስምንት ክልሎች በመተግበር ላይ የሚገኘው የራይዝ ፕሮጀክት ክፍል የሆነው የስማርት ስታርት ትግበራን በተመለከተም ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ ሲፍ እየተስፋፉ የሚገኙ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮጀክት መጀመሩ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።
በቤተሰብ ደረጃ በሲፍ እየተተገበረ የሚገኘው የእናት ፕሮጀክት ሊበረታታ እንደሚገባው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ስርአተ-ምግብን ለማሻሻል የሀገር ውስጥ የምግብ ምርትን ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይት መድረኩ የራይዝ አፕ ፕሮጀክትን ማሳደግ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ከሌሎች ጋር በጥምረት ሊተገበሩ በሚችሉበት መንገድ፣ እንዲሁም “ውሃ ለሁሉም” በሚል እየተተገበረ በሚገኘው ፕሮጀክት ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡