ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየመከሩ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየመከሩ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ በምክክሩ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች እና ምሁራን ተገኝተዋል።
ርዕስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር በክልሉ በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ፣ በቀጣይስ ምን ዓይነት አቅጣጫ መቀመጥ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በሐሰተኛ ትርክት የተፈጠረውን ሃሳብ በማረም ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሰራ አድርጎ መቆየቱንም አመላክተዋል።
አሁን ላይ ክልሉ በተሻለ የሰላም እንቅስቃሴ ላይ መኾኑንም ገልጸው÷ የኮሚሽኑ ተግባራት በአግባቡ እንዲፈጸም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ግጭት የከተተዉን ችግር አጀንዳ በመቅረጽ እና ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ሥራ የሀገሪቱን ሁሉንም አካባቢዎች ማዳረስ እና ችግሮችን መለየት መኾኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ለመድረስ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ሰርተናል ማለታቸውንም አሚኮ ዘግቧል፡፡