በክልሉ የመድሐኒት ይዘት ያላቸው ምግቦች ህገ ወጥ ንግድና ዝውውር ላይ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመድሐኒት ይዘት ያላቸው ምግቦችን ህገ ወጥ ንግድና ዝውውር ላይ የሚመክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
መድረኩ የመድሐኒት ይዘት ያላቸው ምግቦችን ህገ ወጥ ንግድና ዝውውር እንዲሁም አግባብ ያልሆኑ የህፃናት ምግብ ማስተዋወቅ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት በመምከር ለችግሮቹ መፍትሄ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ህፃናት የሚመጣ አልሚ ምግብ በህገ ወጥ መንገድ ወጥቶ በየሱቁ እየተሸጠ በመሆኑ መቆጣጠር እንደሚገባ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጎሮ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር አስገንዝበዋል።
በተያያዘም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጪ ምርት ቁጥጥርና ወቅታዊ የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር ግብረ ሀይል አቋቁሟል።
ግብረ ሀይሉ ሁለንተናዊ የንግድ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠርና የሚከታተል ስለመሆኑ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ተናግረዋል።
በዘርፋ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት ግብረ ሀይሉ፤ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ የሸቀጣሸቀጥና ሌሎች የኮንትሮባንድ ህገ ወጥ ተግባራትን ይቆጣጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ መድሐኒት ነክ ምግቦችን በተመለከተም የቁጥጥር ስራው አንዱ አካል ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በብርሃኑ በጋሻው